ጉሲን እና ቁነና (Physics & Measurement) ክፍል 4፤ የኑሲቃ ብያኔ (Part 4: Definition of the Second)

“What then is time? If no one asks I know; if I want to explain it to a questioner, I do not know.” (St. Augustine)
“እናስ፣ ጊዜ ምንድን ነው?  መልሱን በልቤ ባውቀውም፣ ባንደበቴ ግን አላውቀውም።” (ቅዱስ አውግስጦስ)

አመት ሁለት ዓመት ሲሄድ እያያችሁ
ጊዜ ገሰገሰ ለምን ትላላቸሁ?
በዘመን ግስገሳ እድሚያችን ተማርኮ
ያለፍነው እኛ ነን ጊዜ አይደለምኮ።
(አለቃ ከበደ ሚካኤል)

በቆመ ጊዜ ላይ ራሱ እየዋኘ
ዋናውን ሳያቆም ጊዜን ቁሞ ሊያየው ከንቱ እየተመኘ
ራሱ እየሄደ ጊዜ ሄደ ይላል ሰው እየተሞኘ።

ጊዜ ውቅያኖስ ነው የውሃ ባለፀጋ
በስፋት ተንጣሎ ባለበት የረጋ፣
መልኩ እሚፈራረቅ ሲጨልም ሲነጋ
በክረምት ቀዝቅዞ የሚሞቅ በበጋ
ሐሴት የሞላበት ተከቦ ባደጋ።

ሂወት መዋኘት ነው ውሃ ላይ መንሳፈፍ
እንደ ሂውቱ ዓይነት በተለያየ ዘርፍ
እያወናጨፉ ውሃውን በመቅዘፍ
ከልደት እስከ ሞት በምዕራፎች ማለፍ።

ከማሕፀን ወጥቶ ተገፍትሮ በምጥ
ሰው አንዴ ከገባ ከሰፊው ውሃ ውስጥ፣
ተግቶ በመዋኘት ወይም በማላገጥ
ይቀጥላል እንጅ ትንፋሹ እስኪቋረጥ፣
ፍጡር በመሆኑ ልቡ ስለሚቀልጥ
ውሃውን ሰንጥቆ አልፎ በማቋረጥ
ጊዜን ድል አድርጎ ከጊዜ በመብለጥ
በመሆን የማይሞት ቋሚ እማይለወጥ
ፈጣሪ ዙፋን ላይ አይችልም ሊቀመጥ።

ስለዚህም ዓሣ በውቅያኖስ ዓለም
ምግቡን ለመፈለግ እርሻውን ሲቃርም
ሰውየውን አይቶት ካላረገው ለቀም
ቁርጥም፣ ቁርጥምጥም ከውሃ ጋር ግስም፣
ይዋኝ ይዋኝና ጉልበቱ ሲደክም
እሱ በማቆሙ ጊዜ ለሱ ሲያቆም
ልቡ ቀጥ ብሎ ሲያዝል የረጋ ደም
ከውሃው ሥር አርፎ ይተኛል ዘላለም።

ባጭሩ እስከሚቀጭ ወይ እስከሚጃጅ
በጊዜ ውሃ ላይ በየራሱ ፈርጅ
መዋኘት ይዋኛል ሁሉ ያዳም ልጅ
ትልቁ ቁም ነገር እሱ አይደለም እንጅ።

ቀናችን ሲደርስ ዋናችን ስንፈጽም
ወደመጣንበት ቁልቁል ስንሰጥም
ውሃ ሥር ስንተኛ ላንነሳ መቸም
ሥጋ ሲበሰብስ፣ ሲፈራርስ ዐፅም
ካካላችን ጋራ አብሮ እንዳይከስም
መትጋት ያስፈልጋል ተንሳፎ እንዲቀር ስም።

ለመጠየቅ ያህል በቀልድ እንደ ዘበት፣
ከቃሉ በስተቀር ከወጣው ካንደበት
ሁሉም ስለሚያልፍ በሕጉ መሠረት፣
ይሄ ጊዜ እሚባል ውቅያኖስ ፍጥረት
የሱም ተራ ደርሶ መች ይሆን የሚሞት
ውሃው የሚደርቅ የሚያልቅ በትነት?
(መስፍን አረጋ)

ማሳሰቢያ

ይህ ጦማር (ማለትም ክፍል 4) ሙሉ በሙሉ የተመሠረተው በሚቀድሙት ጦማሮች (ማለትም ከፍሎች 1 እስከ 3)  ላይ ስለሆነ፣ ይህን ክፍል ከማንበብወ በፊት ክፍሎችን 1 እስክ 3 በተለይም ደግሞ ስለ ቁነና ስርካቶች አወቃቀር (construction of measurement systems) የሚያወሳውን ክፍልን 3 ቢያንስ ቢያንስ በገረፍታ ይመልከቱ።

ጊዜ ምንድን ነው? (What is time?)

  1. ጊዜ ምንድን ነው? (what is time? ) የሚለው ጥያቄ ለመመለስ አልተቻይ (impossible) ነው በሚያስብል ደረጃ በጣም አስቸጋሪ ጥያቄ ነው።
  2.  አብዛኛውን ጊዜ፣ ጊዜ (time) የሚባለው ፅንሳብ (concept) ማለትም ፅንሰሐሳብ በብያኔ (definition) ደረጃ ሊገለጽ የሚሞከረው “ጊዜ ማለት የሁንጊቶች የማያቋርጥ የወደፊት ፍሰት ማለት ነው” (time is the continuous, forward flow of events) በማለት ነው። 
  3. የጊዜ ፍላጻ (arrow of time) የሚባለውም ይሄው የጊዜ “የወደፊት ፍሰት”  (forward flow) ነው። 
  4. “ጊዜ የሁንጊቶች የወደፊት ፍሰት ነው” ማለት ግን የጊዜ ብያኔ (definition of time) ነው ከማለት ይልቅ ሁንጊቶች (events) ወደኋላ ሲመለሱ፣ ትልቅ ሰው ተመልሶ ልጅ ሲሆን መቸም ታይተው እንደማይታወቁ መታዘብን (observation) መግለጽ ነው ማለት የበለጠ ትክክልኛነት ይኖረዋል። 
  5. አንዴ የሆነ ነገር ሊደገም ይችል እንደሆን እንጅ ወይም ደግሞ እንዳልሆነ ሊቆጠር ይችል እንደሆን እንጅ፣ አንዳልሆነ ሊሆን አይችልም።  የሆነ ሆይኑ (የሆነ ሁናል) የሚባለውም ለዚሁ ነው።  
  6. በመንታፊነታቸው (plagiarism) ወደር ካልነበራቸው ከጥንታዊ የግሪክ “ፈላስፎች” ውስጥ አንዱ የነበረው አጋቶን (Agathon) ከኑባውያንን የፍልስፍና (Nubian Philosophy) ባሕር ውስጥ አንዷን ጨለፍ አድርጎ የራሱ አስመስሎ በግሪክ ቋንቋ ተናገረ እንደሚባለውም “ፈጣሪ እንኳን ያለፈውን አይቀይርም” (Even god cannot change the past).
  7. የምስቅልቅለት ሕግ (law of entropy) በሚባለው በግለትሒሲን ሁለተኛ ሕግ (the second law of thermodynamics) መሰረት ደግሞ ክስተቶች  (phenomena) “ወደኋላ ሲፈሱ” መቸም የማይታዩት፣ ወደኋላ አንዳይፈሱ የሚከለክላቸው የጉሲን ሕግ (law of physics) ኑሮ ሳይሆን፣ ወደኋላ የመፍሰስ ሐልዘራቸው (probability) ማለትም እድላቸው ከሞላ ጎደል ዳዶ (zero) ማለትም አልቦ በመሆኑ ብቻ ነው። 
  8. ለምሳሌ ያህል የተቀመጠ ዲንጋ በራሱ ወደላይ የማይዘለው እንዳይዘል የሚከለክለው የጉሲን ሕግ (law of physics) ኑሮ ሳይሆን፣ በዲንጋው ውስጥ የሚገኙት፣ በሁሉም አቅጣጫወች (in all directions) በዘፈቀደ (randomly) ውርውር የሚሉት ሁልቆ መሳፍርት የሌላችው ዛልጃኖ (zillion) ፀምሪቆች (molecules) ባንድ ቅጽበት (in one instant) ላይ ባንድ አቅጣጫ  (in one direction) የመንቀሳቀስ እድላቸው ከሞላ ጎደል ዳዶ (zero) ስለሆነ ብቻ ነው።    
  9. አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጊዜ (time) የሚባለው ፅንሳብ (concept) በሦስት ስፍረታዊ ህዋ (three-dimensinal space) ላይ የሚጨመር አራተኛ ስፍረት (fourth dimension) ነው ይባልና፣ አራት ስፍረቶች (four dimensions) ያሉት ህዋጊዜ (space-time) የሚባለው ፅንሳብ (concept) ይፈጠራል።
  10. ለዚህ ምክኒያቱ ደግሞ በህዋ (space) ላይ የሚከሰት ሁሉ በጊዜ (time) ላይ መከሰቱ፣ ማለትም ሁንጊት (event) ሲባል መቸት (where and when) ማለትም መቸ እና የት ያለው መሆኑ ።    
    • አራት ስፍረታዊ ህዋጊዜን (four-dimensional space-time) በስዕል ለማስቀመጥ የህዋን (space) አንዱን ስፍረት መቀነስ (subtract one dimension) ያስፈልጋል። 
    • ከህዋ ሦስት ስፍረቶች (three dimensions) ውስጥ አንዱን ስፍረት በመቀነስ ህዋውን እንዲወክል የሚደረግ ጸጸፍ (a surface with one dimension less than the space it represents) ደግሞ ኦላጸጽፍ (hypersurface) ይባላል። 
    • ጸጸፍ (surface) የሚለው ቃል የተገኘው ጸፍጻፋ (ማለትም ጠፍጣፋ) ከሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን፣ ኦላ (hyper) የሚለው ቃል የተገኘው ደግሞ ኦላና (ከፍተኛ) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ነው። 

ውናቅ (Axiom) እና ውናቃዊ መሠረት (Axiomatic Foundation)

  1. ጊዜ (time)፣ ነጥብ (point)፣ ሕዋ (space)፣ ቁሰት (mass)፣ ሌትሪክ ጸውሪክ (electric charge) እና የመሳሰሉት ፅንሳቦች (concepts) በራሳቸው ግልጽ የሆኑ (self-evident) ፅንሳቦች  (concepts) ማለትም ጥያቄ የማያስፈልጋችው ፅንሳቦች (concepts) ቢሆኑም፣ እንዲህ ናቸው ብሎ በቃላት ለመበየን (define) ግን የማይቻሉ ናቸው።
  2. እንደዚህ ዓይነት በራሳቸው ግልጽ (self-evident) ስለሆኑ ጥያቄ የማያስፈልጋቸው ነገር ግን ሊበየኑ የማይችሉ ፅንሳቦች (concepts) ውናቆች (axioms) ይባላሉ።
  3. ውናቅ (axiom) የሚለው ቃል የተገኘው ውነት እና ሐቅ ከሚሉት ሲሆን፣ ግሱም ሲረባ ወነቀ (axiomize, axiomatize)፣ ውንቅ (ውኑቅ) [axiomized, axiomatized]፣ ወናቂ (axiomizing, axiomatizing)፣ ውነቃ (axiomization, axiomatization)፣ ውንቀት፣ ውናቄ፣ ውናቆሽ እያለ ይሄዳል። 
  4. በሒሳብሲን (mathematics)፣ በጉሲን (physics) እና በሌሎች ሰገሎች (other sciences) ውስጥ ውናቆች (axioms) የሚያገለግሉት እንደ መነሻ ፅንሳብ (starting concepts) በመሆን፣ ሌሎች ከፍተኛ ፅንሳቦችን (higher concepts) በነሱ አንጻር ለመበየን (define) ነው። 
  5. ማናችውም ነገር መነሻ እንዳለው ሁሉ፣ የሒሳብሲን እና የስገል ዘርፎች የሚዋቀሩትም የተወሰኑ ውናቆችን ባካተተ ውናቃዊ መሠረት (axiomatic foundation) ላይ ነው።
  6. ለምሳሌ ያህል በኑባዊ ቂሳሲን (Euclidean geometry) ላይ ነጥብ (point) የሚባለው ፀንሳብ እንደ ውናቅ (axiom) ይወሰድና፣ መስመር (line) ማለት የነጥቦች ቅጥልጥለት ነው ተብሎ በነጥብ አንጻር ይበየናል (defined)።

self-evident = በራስ ግልጽ
axiom = ውናቅ
axiomatic = ውናቃዊ
axiomatic foundation = ውናቃዊ መሠረት
axiomize (axiomatize) = ወነቀ

ናኖመናዊ ሑሰቶች እና የጊዜ ቁነና  (Measurement of Time)

  1. ጊዜ የሚባለውን ፅንሳብ (concept) ለመግለጽ (describe) ወይም ለመበየን (define) አልተቻይ (impossible) ነው በሚያስብል ደረጃ በጣም ከባድ ቢሆንም፣ ጊዜን መቆነን (measure) ማለትም መለካት ግን በዚያው መጠን ቀላል ነው።
  2. በርግጥም በከፍተኛ እቅጭነት (high accuracy) ሊቆነኑ (measured) ከሚችሉት ግኡዝ ናይባወች (physical quantities) ውስጥ አንዱና ዋናው ጊዜ (time) ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ ዝውተራ (frequency) ነው።  
  3. ራሱን በእኩል ጊዜወች ውስጥ የሚደጋግም ማናቸውም ናኖመናዊ ክስተት (periodic phenomenon) ጊዜን ለመቆነን (measure) ሊያገለግል ይችላል።   
  4. ለምሳሌ ያህል የጀዊሳ (pendulum) ጅወሳ፣ ምድር በፀሐይ ዙርያ የምትሖረው ሑረት (revolution)፣ እንዲሁም ምድር በረቲዷ (axis) ላይ የምትሽከረከረው ሽክርከረት (rotation) ወይም ሹረት (spin) ናኖማናዊ ሑሰቶች (periodic motions) ስለሆኑ፣ ጊዜን ለመቆነን ሊያገለግሉ ይችላሉ።  
  1. በዚህ ጦማር ላይ በቤንቤራዊ የቶካዶች ስርካት (International System of Units) ወይም ቤቶስ (SI system) ውስጥ የጊዜ ደርክ ቶካድ (standard unit of time) ስለሆነው ስለ ኑሲቃ (second) አበያየን (definition) እናወሳለን። 
  2. በመጀመርያ ግን ይህን የጊዜን ደርክ ቶካድ (standard unit of time)፣ በተጨማሪ ደግሞ በሚቀጥሉት ሁለት ጦማሮች ላይ የምናወሳቸውን የርዝመት ደርክ ቶካድ (standard unit of length) የሆነውን ሜትርን (meter) እና የቁሰት ደርክ ቶካድ (standard unit of mass) የሆነውን ሃጃኖግራምን (kilogram) ለመበየን (define) የሚስችለንን ወፍቃል (jargon) እንመሠርታለን።
  3. ወፍቃል (jargon) ማለት በሆነ ርዕስ ላይ ለመወያየት ወይም ለመግባባት የሚያስችሉ ቃሎች ስብስብ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ደግሞ የወፍ ቋንቋ ከሚለው ነው። ግሱም ሲረባ ወፈቀለ፣ ውፍቅል፣ ወፍቃሊ (ወፍቃ)፣ ውፍቀላ እያለ ይሄዳል። ወፍቃለኛ (jargonist) ማለት ደግሞ የኔ ቢጤ ማለት ነው።

jargon = ወፍቃል
jargon (verb) = ወፈቀለ
jargonist = ወፍቃለኛ፣ ወፍቃይ

ሰገል ዋሸራ (Science Academy)

  1. በግእዝ ሰገል ማለት ጥበብ ማለት ነው፣ ሰብዓ ሰገል እንዲሉ፣ የጥበብ ሰወች ሊሉ። 
  2. ይህም ሰገል የሚባል ቃል science የሚለውን የንግሊዘኛ ቃል ይተካልናል፣ ጥበብ የሚለውን wisdom ለሚለው በመተው።
  3. ሰገል (science) ከሚለው ቃል ሰገላዊ (scientific)፣ ሰገለኛ (scientist)፣ ሰገላዊ ዘዴ (scientific method) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  4. ዋሸራ ደግሞ ጎጃም ውስጥ የሚገኝ የቅኔ መዘረፊያ ቦታ ስም ነው።  ይህም የታሪካዊ ቦታ ስም academy የሚለውን የንግሊዘኛ ቃል ይተካልናል። 
  5. ዋሸራ (academy) ከሚለው ዋሽራዊ (academic, academical)፣ ዋሸራዊ ነጻነት (academic freedom)፣ ዋሸራዊ ጅረት (academic stream) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  6. ዋሸራ (academy) የሚለውን ጌ (ቦታ) ከሚለው የግእዝ ቃል ጋር በማጣመር ደግሞ ዋሸርጌ (academe) የሚለውን ቃል እናገኛለን። 
  7. ዋሸርጌ (academe) ማለት የዋሸራ አገር፣ የትምህርት ቦታ፣ ከፍተኛ ትምህርት ቤቶች ማለት ነው።
  8. ሰገል ዋሸራ (Science Academy) ማለት ደግሞ በሰገል (science) ጉዳዮች ላይ የሚያተኩርና ስልጣን ያለው የከፍተኛ ሰገለኞች (scientists) ድርጅት እንደማለት ነው፣ የፈረንሳይ የሰገሎች ዋሸራ (French Academy of Sciences) እንዲሉ።

academy = ዋሸራ
academic (academical) =  ዋሸራ፣ ዋሸራዊ
academic freedom = ዋሸራ ነጻነት
academic stream = ዋሸራ ጅረት
academic year = ዋሸራ ዓመት
academician (academist) = ዋሸረኛ፣ ዋሸሬ
academe = ዋሸርጌ
science (scientific) = ሰገል፣ ሰገላዊ
scientist = ሰገለኛ፣ መሰግል
scientific method = ሰገላዊ ዘዴ
science academy =  ሰገል ዋሸራ

ስርካት (System) እና መቅር (Structure)

  1. ስርአት የሚለውን ቃል ለማርባት ይመች ዘንድ በትንሹ በመለወጥ ስርካት (system) የሚለውን ቃል እናገኛለን። ግሱም ሲረባ ሰረከተ (systematize)፣ ስርክት (ስርኩት) (systematized)፣ ሰርካቲ (ሰርካች) [systematizer]፣ ስርከታ (systematization) እያለ ይሄዳል። ሰረከተ (systematize) ማለት ስርካት መሠረተ እንደ ማለት ሲሆን፣ ስርክት (ስርኩት) [systematized] ማለት ደግሞ የተሰረከተ ማለት ነው። 
  2. በተመሳሳይ መንገድ መዋቀር የሚለውን ቃል ለማርባት ይመች ዘንድ በትንሹ በመለወጥ መቅር (structure) እንለዋለን። ግሱም ሲረባ መቀረ (to structure)፣ ምቅር (ምቁር) [structured]፣ መቃሪ (structuring)፣ ምቀራ (structuring) እያለ ይሄዳል። መቀረ (to structure) ማለት መቅር (structure) መሠረተ (አዋቀረ) ማለት ሲሆን፣ ምቅር (ምቁር) [structured] ማለት ደግሞ የተመቀረ (የተዋቀረ፣ ውቅር) ማለት ነው።  
  3. መቅር (structure) ከሚለው ቃል ታሕታይ መቅር (infrastructure, substructure)፣  ላዕላይ መቅር (superstructure)፣ ፊኖ መቅር (fine structure)፣ ኦላፊኖ መቅር (hyperfine structure) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  4. ባማረኛ ፊኖ (fine) ማለት ደቃቅ ማለት ሲሆን፣ ቃሉም ከጣልያንኛ የተወረሰ ነው፣ ፊኖ ዱቄት እንዲሉ።  ግሱም ሲረባ ፈየነ፣ ፍይን (ፍዩን)፣ ፈያኒ (ፈያኝ)፣ ፍየና፣ ፍይነት፣ ፍያኔ ፍያኖሽ እያለ ሲሄድ የንግሊዘኛ አቻ የለውም።  ፈየነ ማለት ፊኖ አደረገ ማለት ሲሆን፣ ፍይን (ፍዩን) ማለት ደግሞ የተፈየነ ማለት ነው።
  5. ፊኖ መቅር (fine structure) እና ኦላፊኖ መቅር (hyperfine structure) የቀኒጦችን የግልበት ጠለሎች (energy levels of atoms) ለመግለጽ የሚያገለግሉ የጉሲን (physics) ስያሜወች ናቸው።

system (systematic) = ስርካት፣ ስርካታዊ
systematize =  ሰረከተ
systematization = ስርከታ፣ አሰረካከት
structure = መቅር
structure (verb) =  መቀረ
structuring = ምቀራ
infrastructure (substracture) = ታሕታይ መቅር
superstructure =  ላዕላይ መቅር
fine = ፊኖ
fine (verb) = ፈየነ
fine structure = ፊኖ መቅር
hyperfine structure = ኦላፊኖ መቅር

ጀዊሳ (Pendulum)

  1. ጀውጃዋ ከሚለው ቃል ጀዊሳ (pendulum) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ጀዊሳ (pendulum) ማለት በክር ወይም በሌላ ነገር ተንጠልጥሎ የሚወዛወዝ አካል (object) ማለት ነው።
  2. የጀዊሳ (pendulum) ግስ ሲረባ ጀወሰ፣ ጅውስ፣ ጀዋሲ (ጀዋሽ)፣ ጅወሳ፣ ጅዋሴ፣ ጅዋሶሽ እያለ ሲሄድ የንግሊዘኛ አቻ የለውም።  ጀወሰ ማለት የጀዊሳ ዓይነት እንቅስቃሴ አደረገ፣ እንደ ጀዊሳ ሆነ ማለት ሲሆን፣ ጅውስ ማለት ደግሞ የተጀወሰ ማለት ነው፣ ጀዊሳውን ጀውሰው እንዲሉ።
  3. ጀዊሳ  (penulum) ተንጠልጥሎ የሚጀውስበት (የሚወዛወዝበት) ነጥብ (point) ናኖት (pivot) ሲባል፣ ቃሉ የተገኘው ደግሞ ወነወነ (ማለትም ወዘወዘ) ከሚለው ቃል ነው። 
  1. አያሌ አይነት ጀዊሳወች (pendulums) አሉ።  ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ ፈናሪ ጀዊሳ (ballistic pendulum)፣ ቶቢናዊ ጀዊሳ (connical pendulum)፣ ቁኝር ጀዊሳ (coupled pendulum)፣ ፉኮ ጀዊሳ (Foucault pendulum)፣ ጥምዘራዊ ጀዊሳ (torsion pendulum, torsional pendulum)፣ ግኡዝ ጀዊሳ (physical pendulum) እና ሰታብ ጀዊሳ (simple pendulum) ናቸው።
  2. ሰታብ ጀዊሳ (simple pendulum) ማለት ከሞላ ጎደል ቁሰትቢስ (massless) ነው ሊባል በሚችል በቀጭን ክር የተንጠለጠለ፣ ስለዚህም መላው ቁሰቱ (all of its mass) የሚውለው በክሩ ጫፍ ላይ በሚገኝ ቱምቢ (bob) በሚባል ትንሽ አካል ላይ የሆነ፣ ጅወሳው (ማለትም ውዝዋዜ) ደግሞ ባንድ ሰቴ (one plane) ላይ የሚውል ጀዊሳ (pendulum) ማለት ነው።
  3. ሰታብ (simple) ማለት ቀላል ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ደግሞ ስልጳ (ቀላል) ከሚለው የወላይተኛ ቃል ነው።  ሰታብ (simple) የወታብ (complex) ማለትም የውስብስብ ተቃራኒ ነው።   
  4. ቶቢናዊ ጀዊሳ (conical pendulum) ማለት ልክ እንደ ሰታብ ጅዊሳ (simple pendulum) ሁኖ የሚጀውሰው ግን ባንድ ሰቴ (one plane) ላይ ሳይሆን ባግዳሚ ክብ (horizontal circle) ላይ የሆነ ጀዊሳ ማለት ነው።   ቶቢናዊ ጀዊሳ (connical pendulum) የተባለበት ምክኒያት ደግሞ ቱምቢው (bob) ባግዳሚው ክብ ላይ ሲዞር፣ ቱምቢው የተንጠለጠለበት ክር የቶቢን (cone) ቅርጽ ስለሚሠራ ነው።
  5. ግኡዝ ጀዊሳ (physical pendulum) ማለት ባንድ ሰቴ  (one plane) ላይ የሚጀውስ ማናቸውም ግኡዝ አካል (physical object) ማለት ነው።  ስለዚህም ሰታብ ጀዊሳ (simple) የግኡዝ ጀዊሳ (physical pendulum) ልዩ ረገድ (special case) ነው ማለት ነው።   

ናኖመን (Period) እና ዝውተራ (Frequency) 

  1. የምድር በፀሐይ ዙርያ መዞርን፣ የምድር በረቲዷ (axis) ላይ መሽከርከርን (rotate) ወይም የጀዊሳ (pendulum) መጀወሰን (oscillate) የመሰለ በእኩል ጊዜወች ውስጥ የሚደጋገምን ክስተት (phenomenon) እናጢን።
  2. ክስተቱ አንድ ሙሉ ኡደት (one full cycle) ለማጠናቀቅ የሚፈጅበት ጊዜ (time) የክስተቱ ናኖመን (period) ይባላል። 
  3. ክስተቱ በተወሰነ ጊዜ ውስጥ የሚያጠናቅቃቸው ሙሉ ኡደቶች ቁጥር (number of full cycles) ደግሞ ክስተቱ በዚያ ጊዜ ውስጥ ያለው ዝውተራ (frequency) ይባላል። 
  4. ናኖመን (period) የሚለው ቃል የተገኘው ናኖ (ማለትም ክብ፣ ዙር) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል እና ዘመን ከሚለው ያማረኛ ቃል ነው። 
  5. ዝውተራ (frequency) የሚለው ቃል የተገኘው ደግሞ አዘወተረ (ማለትም ተመላለሰ) ከሚለው ቃል ነው። 
  6. ለምሳሌ ያህል አንድ ሰታብ ጀዊሳ (simple pendulum) ካንደኛው ጫፍ ተነስቶ፣ ሌላኛው ጫፍ ደርሶ ወደ ተነሳበት ጫፍ ለመመለስ፣ ማለትም አንድ ሙሉ ኡደት (one full cycle) ለመፈጸም የሚፈጀው ገማሽ ኑሲቃ (0.5 second) ነው እንበል።
    • ይህ ግማሽ ኑሲቃ (0.5 second) የጀዊሳው ናኖመን (period of the pendulum) ነው።
    • ጀዊሳው አንድ ሙሉ ኡደት (one full cycle) ለመፈጸም ግማሽ ኑሲቃ (0.5 second) ይፈጅበታል ማለት ደግሞ ባንድ ኑሲቃ ውስጥ (in one second)  ሁለት ሙሉ ኡደቶችን (two full cycles) ያጠናቅቃል ማለት ነው። 
    • ስለዚህም የጀዊሳው ዝውተራ (frequency) ሁለት ኡደቶች በኑሲቃ (two cycles per second) ነው ማለት ነው። 
  7. ባጠቃላይ አነጋገር ደግሞ ያንድ ክስተት ናኖመን (period) ከታወቀ፣ የክስተቱ ዝውተራ (frequency) የናኖመኑ ደባስ (reciprocal) ማለትም ግልብጥ ይሆናል።  ደባስ (reciprocal) የሚለው ቃል የተገኘው ደቢሱ (መገልበጥ) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ነው።

ምነቃ (Oscillation) እና ርግብገባ (Vibration)

  1. ባማረኛ መነቀ ማለት ወዘወዘ፣ ነቀነቀ ማለት ነው፣ መናቃ ወይም ምንቂያም እንዲሉ ወረግራጋ ሊሉ።  ይህም ቃል oscillate የሚለውን የንግሊዘኛ ቃል ይተካልና።  ግሱም ሲረባ መነቀ (oscillate)፣ ምንቅ (ምኑቅ) [oscillated]፣ መናቂ (oscillating, oscillatory)፣ ምነቃ (oscillation)፣ ምንቀት፣ ምናቄ፣ ምናቆሽ እያለ ይሄዳል።
  2. ተርገበገበ (vibrate) ማለት ተወዛወዘ፣ ንቀጠቀጠ፣ ተንዘፈዘፍ ማለት ነው።  ከዚህም ርግብገባ (vibration)፣ ርግብገባ ሑስት (vibratory motion) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  3. ምነቃ (oscillation) ማናቸውንም የወዲያ ውዲህ (back and forth) እንቅስቃሴ የሚገልጽ ቃል ሲሆን፣ ርግብገባ (vibration) ደግሞ የተናቃናቂውን አካል መለጠጥ (stretching) ወይም መጉበጥ (bending) የሚያስከትል የመንዘፍዘፍ እንቅስቃሴ ነው።   

ተጓዥ ሞገድ (Travelling Wave) እና ሞግርመት (Wavelength) 

  1. ተጓዥ ሞግድ (travelling wave) ማለት ቁስን (matter) አውኮ (disturb) እንዲመንቅ (oscillate) በማድረግ በምነቃው (oscillation) አምካኝነት ጉልበትን (energy) ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚያጓጉዝ ሁከት (disturbance) ማለት ነው።  
  2. ለምሳሌ ያህል ኩሬ ላይ በተወረወረ ዲንጋ የሚፈጠር የውሃ ሞገድ (water wave) ውሃውን ከፍ፣ ዝቅ እያደረገ በማወዛወዝ ውዝዋዜውን በሁሉም አቅጣጫ ይነዛዋል።
  3. የተጓዥ ሞገድ (travelling wave) ዠከፍተኛ ነጥብ (highest point) ማለትም ከሁሉም በላይ የሆነው ነጥብ፣ የሞገዱ ደበጥ (crest) ሲባል፣ የሞገዱ ዠዝቅተኛ ነጥብ (lowest point) ማለትም ከሁሉም በታች የሆነው ነጥብ ደግሞ የሞገዱ ዘፈጥ (trough) ይባላል።
  4. ደበጥ (crest) የሚለው ቃል የተገኘው ደግሞ ዲብ (ማለትም ጎራ) ከሚለው ቃል ሲሆን፣  ዘፈጥ (trough) የሚለው ቃል የተገኘው ደግሞ ዘፍ አለ፣ እንደ ዛፍ ወደቀ ከሚለው ነው። 
  5. በማናቸውም ተጓዥ ሞገድ (travelling wave) ላይ በሁለት ተከታታይ ደበጦች (two consecutive crests) ወይም በሁለት ተከታታይ ዘፈጦች (two consecutive troughts) መካከል ያለው ርርቀት (distance) የሞገዱ ሞገድርዝመት (wavelength) ወይም ባጭሩ ሞግርመት (wavelength) ይባላል። 

ክስተት (Phenomenon)፣ ሁንጊት (Event) እና ፅንሳብ (Concept)

  1. ሁነት እና ድርጊት ከሚሉት ቃሎች ሁንጊት (event) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ሁንጊት (event) ማለት የሚሆን (የሆነ) ነገር፣ ድርጊት፣ ክስተት እንደ ማለት ነው።
  2. የሁንጊት (event) ግስ ሲረባ ሆነገተ፣ ሁንግት፣ ሆንጋቲ (ሆንጋች)፣ ሁንገታ፣ ሁንጋቴ፣ ሆንጋቶሽ እያለ ሲሄድ፣ የንግሊዘኛ አቻ የለውም።
  3. ክስተት (phenomenon) ተከሰተ እንደምንለው፣ ሁንጊት ሆነገተ እንላለን።
  4. ፅንሰ ሐሳብ የሚለውን ለማርባት ይመች ዘንድ በማሳጥር ፅንሳብ (concept) እንለዋለን።  ግሱም ሲረባ ፀነሰበ (conceptualize)፣ ፅንስብ (ፅንሱብ) [conceptualized]፣ ፀንሳቢ (conceptualizing)፣ ፅንሰባ (conceptualization)፣ ፅንስበት፣ ፅንሳቤ፣ ፅንሳቦሽ እያለ ይሄዳል።
  5. ፀነሰበ (conceptualize) ማለት ፅንሳብ መሠረተ ማለት ሲሆን፣ ፅንስብ (ፅንሱብ) [conceptualized] ማለት ደግሞ የተፀነሰበ ማለት ነው።   

phenomenon = ክስተት
event = ሁንጊት
event (verb) = ሆነገተ
concept = ፅንሳብ
conceptualize = ፀነሰበ
conceptualization = ፅንሰባ

ትናማ (Past)፣ አሁማ (Present) እና ነጉማ (Future) 

  1. ትናንት (yesterday) ከሚለው ትናማ (past) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ትናማ (past) ማለት ያለፈው ጊዜ፣ የትናንቱ ጊዜ ማለት ነው።
  2. አሁን (now) ከሚለው አሁማ (present) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  አሁማ (present) ማለት ያሁኑ ጊዜ፣ የዛሬው ጊዜ ማለት ነው።
  3. ነገ (tomorrow) ከሚለው ነጉማ (future) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ነጉማ (future) ማለት መጭው ጊዜ፣ የነገው ጊዜ ማለት ነው። 
  4. ለምሳሌ ያህል “To understand your present look at your past, to know your future look at your present” የሚለውን የቡድሃናኞች (Buddhist) ብሂል “አሁማህን ለመረዳት ትናማህን፣ ነጉማን ለማወቅ ደግም አሁማህን ተመልከት” እንለዋለን።   

ፍዳግ (Error) እና ስርካታዊ ፍዳግ (Systematic Error)

  1. ባማረኛ ገደፈ ማለት ረሳ፣ ተወ፣ ሳተ፣ ዘለለ፣ መስፍን የሚለውን መስን ብሎ ጻፈ ማለት ነው።  ይህን ቃል በመገልበጥ ደግሞ ፍዳግ (error) የሚለውን ቃል እናገኛለን።
  2. ፍዳግ (error) ማለት ስሕተት እንደ ማለት ሲሆን፣ ግሱም ሲረባ ፈደገ (err)፣ ፍድግ (ፍዱግ) [erred]፣ ፈዳጊ (erring)፣ ፍደጋ (erring)፣ ፍድገት፣ ፍዳጌ፣ ፍዳጎሽ እያለ ይሄዳል።
  3. ለምሳሌ ያህል መሳሳት ሰውኛ ነው የሚለው መፈደገ ሰውኛ ነው (to err is human) ሊባል ይችላል። 
  4. የቁነና ፍዳግ (error of measurement) ማለት ከቁነናው የሚገኘው እሴት (value from measuremnt) ከእውነተኛው እሴት (true value) ያለው ርቀት ወይም ፍንገጣ (deviation) ማለት ነው።  ይህ ርቀት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የሚገለጸው ደርክ ፍንገጣ (standard deviation) በሚባል እሴት (value) ነው።
  5. የቁነና ስርካታዊ ፍዳግ (systematic error) ማለት የቁነናውን እሴት (value of measurement) ከእውነተኛው እሴት (true value) ባንድ  በኩል ብቻ በመግፋት ሁልጊዜም የሚያሳንስ ወይም ሁልጊዜም የሚያስበልጥ፣ በቁነና ስርካቱ (system) ውስጥ ወይም በቁነናው ሂደት ላይ በተሰነቀረ ሕፅፅ ሳቢያ የሚከሰት ፍዳግ (error) ማለት ነው።  
  6. ለምሳሌ ያህል ከዳዶ ኑሲቃ (zero second) መነሳት ሲገባው ከ 0.5 ኑሲቃ (0.5 second) የሚነሳ የቆይታ መለኪያ፣ የሁሉንም ቆይታወችን መጠኖች በ 0.5 ኑሲቃ ከፍ በማድረግ በልካቶቹ ላይ ስርካታዊ ፍዳግ (systematic error) ይፈድጋል ማለትም ይፈጥራል። 

err = ፈደገ
error = ፍዳግ
error analysis = ፍዳግ ትንተና
error function = ፍዳግ ቀዘድ
standard deviation = ደርክ ፍንገጣ
trial and error = ሙከራና ፍዳግ
systematic error = ስርካታዊ ፍዳግ

እቅጭነት (Accuracy) እና ጭሃነት (Precision)

  1. ባማረኛ እቅጩን ማለት እርግጡን ማለት ነው፣ እቅጩን ተናገር እንዲሉ።  ከዚህም እቅጭ (accurate, exact)፣ እቅጭነት (accuracy, exactness) የሚሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  2. ባማረኛ ጭሃ ማለት ትክክል፣ እልፍ፣ ትርፍ የሌለው ማለት ነው።  ጭሃ (accurate)፣ ጭሃነት (accuracy) የሚሉትን ቃሎች እናገኛለን።  
  3. እቅጭነት (accuracy) እና ጭሃነት (precision) ተመሳሳይ ቃሎች ቢሆኑም በመጠኑ የተለያዩ ናቸው።
  4. የቁነና እቅጭነት (accuracy of measurement) ከቁነናው (measurement) የሚገኘው እሴት (value) ለእውነተኛው እሴት (true value) ያለውን ቅርበት (closeness) መግለጫ ነው።
    • የበለጠ ከፍተኛ እቅጭነት (high accuracy) ያለው ቁነና (measurement) የሚሰጠው እሴት ለእውነተኛው እሴት የበለጠ የቀረበ ነው።
    • በሌላ አባባል ከፍተኛ እቅጭነት (high accuracy) ያለው ቁነና (measurement) ፍዳጉ (error) በዚያው መጠን ዝቅተኛ ነው። 
  5. በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ቁነና ከፍተኛ ጭሃነት (high precision) አለው ማለት ቁነናው ሲደጋገም የሚሰጣቸው እሴቶች (values) ከሞላ ጎደል ያውቴ  (same) ናቸው ማለት ነው፣ እሴቶቹ ከእውነተኛው እሴት (true value) የራቁ ሊሆኑ ቢችሉም። 
    • በዚህም ምክኒያት ከፍተኛ ጭሃነት (high precision) ያለው ቁነና (measurement) ከፍተኛ ተራቢነት (high reproducibility) ወይም ተደጋጋሚነት አለው ይባላል። 
    • ስለዚህም የቁነና ጭሃነት (precision of measurement) የሚገልጸው የቁነናውን እቅጭነት (exactness) ሳይሆን የቁነናውን ተራቢነት (reproducibility) ወይም ተደጋጋሚነት ነው ማለት ነው።
    • ሆኖም ግን  ጭሃ (precise) ቁነናወች አብዛኛውን ጊዜ እቅጭ (exact) ስለሆኑ፣ እቅጭነት (exactness) እና ጭሃነት (precission) አብዛኛውን ጊዜ የሚወሰዱት ተመሳሳይ እንደሆኑኑና ሊለዋወጡ እንደሚችሉ ቃሎች ነው።   

accurate (exact) = እቅጭ
accuracy (exactness)  = እቅጭነት
precise  = ጭሃ
precision (exactness) =  ጭሃነት
reproduce = አረባ
reproducibility = ተራቢ፣ ተራቢነት

ደርክ (Standard) እና ደርክ ቶካድ (Standard Unit)

  1. ደረጃ ከሚለው ደርክ (standard) የሚለውን ቃል እናገኛለን። 
  2. ደርክ (standard) ማለት ደረጃ ወይም ማነጻጸርያ እንደ ማለት ሲሆን፣ ግሱም ሲረባ ደረከ (standardize)፣ ድርክ (ድሩክ) [standardized]፣ ደራኪ (standardizing)፣ ድረካ (standardization)፣ ድራኬ፣ ድራኮሽ እያለ ይሄዳል።
  3. ደረከ (standardized) ማለት ደርክ መሠረተ ማለት ሲሆን፣ ድርክ (ድሩክ) [standardized] ማለት ደግሞ የተደረከ ማለት ነው። 
  4. ደርክ ቶካድ (standard unit) ማለት ደግሞ ለመቆነን (measure) የሚያገለገል ሲማካዊ ቶካድ (basic unit) ማለት ነው፣ የጊዜ ደርክ ቶካድ (standard unit of time)፣ የርዝመት ደርክ ቶካድ (standard unit of length)፣ የቁሰት ደርክ ቶካድ (standard unit of mass) እንዲሉ።   

standard = ደርክ
standardize = ደረከ
standardization =  ድረካ
standard unit of time  =  የጊዜ ደርክ ቶካድ
standard unit of length = የርዝመት ደርክ ቶካድ
standard unit of mass  = የቁሰት ደርክ ቶካድ

ቃቢሳ (Clock) እና ጨዳሚ (Radio)

  1. አቃቤ ስዓት (ማለትም ሰዓት ጠባቂ) ከሚለው ቃቢሳ (clock) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ቃቢሳ (clock) ማለት ሰዓት በተለይም ደግሞ የጴዛ ሰዓት ወይም የግድግዳ ሰዓት ማለት ነው።
  2. ቃቢሳ (clock) ከሚለው ቀኒጣዊ ቃቢሳ (atomic clock)፣ ቃቢስያ (clockwise)፣ ኢቃቢስያ (anticlockwise, counterclockwise) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  3. ጨረር እና ድምጽ ከሚሉት ጨዳሚ (radio) የሚለውን ቃል እናገኛለን።  ጨዳሚ (radio) ማለት ደግሞ ሬዲዮ ማለት ነው።
  4. የጨዳሚ (radio) ግስ ሲረባ ጨደመ፣ ጭድም (ጭዱም)፣ ጨዳሚ፣ ጭደማ እያለ ሲሄድ፣ የንግሊዘኛ አቻ የለውም። 
  5. ለምሳሌ ያህል ንግግሩ ይጨደማል ማለት ንግግሩ በሬድዮ ይተላለፋል ማለት ነው።
  6. ጨዳሚ (radio) ከሚለው ጨዳሚ ሞገድ (radio wave)፣ ጨዳሚ ሩፓይፋ (radio telescope)፣ ጨዳሚ ቀርኒና (radio antenna) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  7. ሩፓይፋ (telescope) የሚለው ቃል የተገኘው ሩ (tele) ከሚለው ፊልጡፍ (prefix) እና ፓይፋ (scope) ከሚለው ኋልጡፍ ነው። 
  8. ሩ (tele) የሚለው ፊልጡፍ የተገኘው ሩቅ ከሚለው ቃል ሲሆን፣ ፓይፋ (scope) የሚለው ኋልጡፍ የተገኘው ደግሞ አይፊያ (ዓይን) ከሚለው የወላይትኛ ቃል ነው።
  9. በተመሳሳይ መንገድ ጢኖፓይፋ (microscope)፣ ምንቃፓይፋ (oscilloscope)፣ ዳውሮፓይፋ (gyroscope) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።
  10.  ቀርኒና (antenna) የሚለው ቃል የተገኘው ቀርን (ቀንድ) ከሚለው የግእዝ ቃል ነው።

clock = ቃቢሳ፣ ሰዓት
clockwise = ቃቢስያ፣ ሰዓትያ
anticlockwise (counterclockwise) = ኢቃቢስያ፣ ኢሰዓትያ
atomic clock = ቀኒጣዊ ቃቢሳ
radio = ጨዳሚ
radio (verb) = ጨደመ
radio wave = ጨዳሚ ሞገድ

ረፈጥ (Stationary)

  1. ረፈጠ (ወዘፈ፣ አስቀመጠ) ከሚለው ያማረኛ ቃል ረፈጥ (stationary) የሚለውን ቃል እናገኛለን።
  2. ረፈጥ (stationary) ማለት ካለበት የማይንቀሳቀስ፣ ባለበት የተወዘፈ፣ ማለትም ቅምጠቱን (position) የማይለወጥ ማለት ነው።
  3. ግሱም ሲረባ ረፈጠ፣ ርፍጥ (ፍፉጥ)፣ ረፋጢ (ረፋጭ)፣ ርፈጣ፣ ርፍጠት፣ ርፋጤ፣ ርፋጦሽ እያለ ሲሄድ፣ የንግሊዘኛ አቻ የለውም።
  4. ረፈጠ ማለት ረፈጥ ሆነ ወይም አደረገ ማለት ሲሆን፣ ርፍጥ ማለት ደግሞ የረፈጠ ወይም የተረፈጠ ማለት ነው።
  5. ረፈጥ (stationary) ወይም ርፍጥ (stationary) ከሚለው ቃል ጅጋርፍጥጥ ምሕዋር (geostationary orbit)፣ ጅጋርፍጥ አጊና (geostationary satellite) የመሳሰሉትን ቃሎች እናገኛለን።  
  6. ጅጋርፍጥ አጊና (geostationary satellite) ማለት ከምድር አኳይ (equator) በላይ ቅምጠቷን ሳትቀይር ባንድ የሰማይ ነቁጥ ላይ ሳትንቀሳቀ ተንጠልጥላ የቆመች የምትመስል አጊና (satellite) ማለት ነው።
  7. ጅጋርፍጥ ምሕዋር (geostationary orbit) ማለት ደግሞ የጀጋርፍጥ አጊና ምሕዋር (orbit) ማለት ነው። 
  8. አጊና (satellite) የሚለው ቃል የተገኘው አጊና (ጨረቃ) ከሚለው የወላይትኛ ቃል ነው።

stationary = ረፈጥ፣ ርፍጥ
stationarity = ረፈጥነት፣ ርፍጠት
stationary (verb) = ረፈጠ
geostationary orbit = ጅጋርፍጥ ምሕዋር
geostationary satellite = ጅጋርፍጥ አጊና

የምድር እንቅስቃሴ ከፀሐይ (Sun) እና ከሩቅ ኮኮቦች (Distant Stars) አንጻር

  1. ምድር ከፀሐይ ያላት ርቀት በብርሃን ፍጥነት አንጻር ሲገለጽ 8 ደቂቃ (8 minutes) ብቻ ነው።  በሌላ አባባል ብርሃን ከፀሐይ ተነስቶ ምድር ለመድረስ የሚፍጀበት ጊዜ 8 ደቂቃ ብቻ ነው። 
  2. በሌላ በኩል ደግሞ ሰሬ (Sirius) ወይም ውሻ ኮኮብ (Dog Star) የሚባለውን ከሁሉም የሰማይ ኮኮቦች የበለጠ ብሩህ (the brightest star in the sky) የሆነውን ኮኮብ እንውሰድ።  ሰሬ ማለት በኦሮምኛ ውሻ ማለት ነው።
  3. ብርሃን ከሰሬ (Sirus) ተነስቶ ምድር ለመድረስ የሚፈጅበት ጊዜ 8.6 ዓመት ወይም 4.5 ካልጃኖ ደቂቃ (4.5 million minutes) ነው። 
  4. ይህ ማለት ደግሞ ሰሬ ከምድር ያለው ርቀት ፀሐይ ከምድር ያላትን ርቀት 565 ሺ ጊዜ ይበልጣል ማለት ነው።
  5. ስለዚህም ምድር በፀሐይ ዙርያ ስትዞር የምትጓዘው ርቀት፣ ምድር ከሰሬ ካላት ርቀት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት ስለሆነ፣ ምድር ከሰሬ አንጻር እንደማትንቀሳቀስ ተድረጎ ሊወሰድ ይችላል ማለት ።
  6. በሌላ አባባል ከፀሐይ አንጻር ስትታይ ምድር በፀሐይ ዙርያ ብትዞርም፣ ከሰሬ አንጻር ስትታይ ግን ምድር ካለችበት የማትንቀሳቀስ ማለትም ቅምጠቷን (position) የማትለውጥ ረፈጥ (stationary) ወይም ርፍጥ ናት ብሎ በከፍተኛ ቅርበዛ (very high approximation) መናገር ይቻላል ማለት ነው። 
  7. አብዛኞቹ ሩቅ ኮኮቦች (distant stars) ደግሞ ከምድር ያሏቸው ርቀቶ በመቶ እንዲሁም በሺ የብርሃን ዓመታት የሚቆጠር ነው።  ይህ ደግሞ ምድር ከሩቅ ኮኮቦች አንጻር ረፈጥ (stationary) ናት የሚለውን ቅርበዛ (approximation) የበለጠና የበለጠ ትክክለኛ ያደረገዋል።
  8. ምድር ከሩቅ ኮኮቦች አንጻር ረፈጥ (stationary) የምትመስልበትን ሁኔታ በሚከተለው ምሳሌ መረዳት ይቻላል።  አንድ አሞራ ባናታችን ላይ ስታልፍ በጣም ፈጣን ትመስለናለች።   አሞራዋ ከኛ በጣም ርቃ ወደ አድማስ ስትጠጋ ግን፣ የምትንቀሳቀስ አይመስለንም።  ለዚህ ምክኒያቱ ደግሞ አሞራዋ በፍጥነቷ ሳቢያ የምትጓዘው ርቀት፣ ከኛ ካላት ርቀት ጋር ሲነጻጸር ኢምንት በመሆኑ ነው።
  9. በሌላ በኩል ግን ምድር ከሩቅ ኮኮቦች አንጻር ረፈጥ (stationary) ብትሆንም፣ ማለትም ቅምጠቷን (position) ባትለውጥም፣ በረቲዷ (axis) ማለትም በዛቢያዋ ላይ ግን ከፀሐይም ከሩቅ ኮኮቦችም አንጻር ትፎራለች (spin)፣  ፉረት (spin) ማለት አቅጣጫን መለወጥ ማለት ነውና።        

አድማስ (Horizon) እና አናትማስ (Zenith)

  1. ባማረኛ አድማስ (horizon) ማለት ሰማይና ምድር የሚገናኙበት የምድር ዳር ድንበር ማለት ነው፣ ከአድማስ እስከ አድማስ እንዲሉ። 
  2. አናት እና አድማስ ከሚሉት አናትማስ (zenith) የሚለውን ቃል እናገኛለን።   አናትማስ (zenith) ማለት ባናት ትክክል ማለት ነው። 
  3. እግረመንገዳችንን ደግሞ አግዳሚ ዙር ከሚለው አግዙር (azimuth) የሚለውን ቃል፣ ዲሪና (ከፍታ) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ደግሞ ዲሪንሳ (altitude) የሚለውን ቃል እናገኛለን። 

ጀንበራዊ ዕለት (Solar Day) እና ኡርጃዊ ዕለት (Sidereal Day)

  1. በምድር ላይ ዕለት (day) ሲባል ቀን (daytime, day time) እና ሌት (nighttime, night time) ተብሎ በሁለት እኩሌታወች (ማለትም ግማሾች) ይከፈላል። 
  2. ቀን ማለት ባብዛኛው ብርሃን የሆነው (ማለትም ፀሐይ ካድማስ በላይ የሆነችበት) የዕለት ግማሽ ሲሆን፣ ሌት ማለት ደግሞ ባብዛኛው ጨለማ የሆነው (ማለትም ፀሐይ የጠለቀችበት) የዕለት ግማሽ ነው።  ሌት የሚለው ቃል የተገኘው ሌሊት የሚለውን በማሳጠር ነው።  
  3. የምድር የዕለት ርዝመት (length of the day) የሚወሰነው ምድር በፉረት ረቲዷ (rotation axis) ማለትም በሽክርክረት ዛቢያዋ ላይ እንደ እንዝርት እየተሽከረከረች እቅጩን አንድ ሙሉ ፉረት (rotation) ለመፉረር በሚፈጅባት ጊዜ ነው።  ይህ ጊዜ ደግሞ የምድር ፉረታዊ ናኖመን (rotational period) ይባላል። 
  4. በሌላ አባባል ዕለት ማለት የምድር ፉረታዊ ናኖመን ማለት ነው።  ናኖመን (period) ማለት ክፍለ ጊዜ ማለት ሲሆን፣ ቃሉ የተገኘው ደግሞ ናኖ (ክብ) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል እና ዘመን ከሚለው ቃል ነው።
  5. የምድር የዕለት ርዝመት ፀሐይን መሠረት በማድረግ ወይም ሩቅ ኮኮቦችን መሠረት በማድረግ እንደመለካቱ ይለያያል።
  6. ፀሐይን መሠረት በማድረግ የሚለካ የምድር ዕለት ጀንበራዊ ዕለት (solar day) ይባላል።
  7. ሩቅ ኮኮቦችን መሠረት በማድረግ የሚለካ የምድር ዕለት ደግሞ ኡርጃዊ ዕለት (sidereal day) ይባላል።   ኡርጃዊ (sidereal) የሚለው ቃል የተገኘው ኡርጂ (ማለትም ኮኮብ) ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ነው።  
  8. ጀንበራዊ ዕለት (solar day) ማለት ምድር ላይ በቆመ ነጻሪ (observer) አመለካከት ፀሐይ በተከታታይ እቅጩን ካናት በላይ ማለትም አናትማስ (zenith) ላይ ለመሆን የሚፈጅባት ጊዜ ነው። 
  9. በተመሳሳይ መንገድ ኡርጃዊ ዕለት (sidereal day) ማለት ምድር ላይ በቆመ ነጻሪ (observer) አመለካከት አንድ ሩቅ ኮኮብ (distant star) በተከታታይ እቅጩን ካናት በላይ ለመሆን የሚፈጅባት ጊዜ ነው። 
  10. የጀንበራዊ ዕለትና የኡርጃዊ ዕለት ርዝመቶች የተለያዩ የሆኑበት ምክኒያት ምድር በፀሐይ ዙርያ ስለምትሖር፣ ከሩቅ ኮኮቦች አንጻር ግን  ረፈጥ (stationary) ስለሆነች ነው።  
  11. ይህ መሆኑን ደግሞ በሚከተለው ሱርፊክ (figure) ላይ መመልከት ይቻላል።
  1. ምድር በፀሐይ ዙርያ በምታደርገው ሑረት (revolution) ሳቢያ ቅምጠት (position) A ላይ ስትሆን፣ ፀሐይና የሆነች ሩቅ ኮኮብ እንበል ሰሬ (Sirius) እቅጩን ከምድራዊ ነጻሪ አናት በላይ ናቸው እንበልና ጊዜ መቁጠርን ከዚህ ቅምጠት እንጀመር።
  2.  ምድር በረቲዷ (axis) ማለትም በዛቢያዋ ላይ እየፎረረች (rotate) እንዲሁም በፀሐይ ዙርያ እየሖረች (revolve) ቅምጠት (position) B ላይ ስትደርስ፣ ሩቋ ኮኮብ ሰሬ ተመልሳ እቅጩን ከምድራዊው ነጻሪ አናት በላይ ሆነች እንበል። 
  3. ስለዚህም ምድር ከቅምጠት A ተነስታ ቅምጠት B ለመድረስ የሚፈጅባት ጊዜ ኡርጃዊ ዕለት (sidereal day) ይሆናል ማለት ነው።  
  4. ምድር ቅምጠት B ላይ በምትሆነበት ጊዜ ሰሬ እቅጩን ከምድራዊ ነጻሪ አናት በላይ ብትሆንም፣ ፀሐይ ግን አትሆንም፣ ምክኒያቱም ምድር ከፀሐይ አንጻር በመንቀሳቀሷ ሳቢያ ምድራዊው ነጻሪ ፀሐይን የሚመለከትበት አቅጣጫ ተቀይሯልና።
  5. ፀሐይ እቅጩን ከምድራዊው ነጻሪ አናት በላይ የምትሆነው፣ ምድር ቅምጠት B ከደረሰች በኋላ ተጨማሪ ርቀት ተጉዛ ቅምጠት C ላይ ስትደርስ ነው። 
  6. ስለዚህም ምድር ከቅምጠት A ተነስታ ቅምጠት C ለመድረስ የሚፈጅባት ጊዜ ጀንበራዊ ዕለት (Solar day) ይሆናል ማለት ነው።
  7. ስለዚህም በኡርጃዊ ዕለት (sidereal day) እና በጀንበራዊ ዕለት (solar day) መካከል ያለው የጊዜ ልዩነት ምድር ከቅምጠት B ተንሰታ ቅምጥት C ለመድረስ የሚፍጅባት ጊዜ ነው ማለት ነው።
  8. የኡርጃዊ ዕለት (sidereal day) ርዝመት ምድር ከቅምጠት A እስከ ቅምጠት B በምትጓዝበት ፍጥነት (speed) ላይ ይወሰናል።
  9. የጀንበራዊ ዕለት (solar day) ርዝመት ደግሞ ምድር ከቅምጠት A እስከ ቅምጠት C በምትጓዝበት ፍጥነት (speed) ላይ ይወሰናል።
  10. የኬፕለር የፈለክ ሑስት ሕጎች (Kepler’s Laws of Planetary Motion) በሚለው ጦማር (article) ላይ በሰፊው እንደተወሳው ደግሞ ምድር በፀሐይ ዙርያ የምትሖርበት ምሕዋር (orbit) ፍጹም ክብ (perfect circle) ሳይሆን በተወሰነ ደረጃ ሙለት ያለው ፉንባ (ellipse) በመሆኑ ሳቢያ፣ ምድር በፀሐይ ዙርያ የምትጓዝበት ፍጥነት (speed) ቋሚ (constant) ሳይሆን በተወሰነ መጠን የሚለዋወጥ ጠዋጢ (variable) ነው።
  11.  ምድር በሞላላ ምሕዋሯ ላይ ስትሖር (revolve) ለፀሐይ እየቀረበች ስትሄድ ፍጥነቷ እየጨመረ፣ ከፀሐይ እየራቀች ስትሂድ ደግሞ ፍጥነቷ እየቀነሰ ይሄዳል፣ ምንም እንኳን ጭምረቱና ቅንሰቱ እጅግ አነስተኛ ቢሆንም።  
  12. በዚህም ምክኒያት የኡርጃዊ ዕለት እና የጀንበራዊ ዕለት ርዝመቶች ምድር ለፀሐይ እየቀረበች ስትሄድ እየቀነሱ፣ ከፀሐይ እየራቀች ስትሄድ ደግሞ እየጨመሩ ይሄዳሉ ማለት ነው፣ ምንም እንኳን ቅንሰታቸውና ጭምረታቸው እጅግ አነስተኛ ቢሆንም።
  13. የጀንበራዊ ዕለት ርዝመት የኡርጃዊ ዕለት ርዝመትን በቅርበዛ (approximately) 4 ደቂቃ (4 minutes) ገደማ ይበልጣል። 
  14. ይህ ማለት ደግሞ ባንድ ምሽት ላይ ከፀሐይ ጋር እቅጩን አብራ (ባንድነት) ከምሥራቅ አድማስ የወጣች ኮኮብ፣ በሚቀጥለው ምሽት ላይ ከምሥራቅ አድማስ የምትወጣው 4 ደቂቃ ቀድማ ነው ማለት ነው። ምሽት ሰማይ ላይ የሚታዩት ኮኮቦች ከወቅቶች ጋር የሚለዋወጡት በዚህ ምክኒያት ነው። 

አማካይ ጀንበራዊ ዕለት (Mean Solar Day)

  1. በምድር ሑረታዊ ፍጥነት (orbital speed) መለዋወጥ፣ ማለትም ምድር ፀሐይን በምትሖርበት ፍጥነት መለዋወጥ ሳቢያ የኡርጃዊ ዕለት (sidereal day) እና የጀንበራዊ ዕለት (solar day) ርዝመቶች (lengths) ከወቅቶች (seasons) ጋር እንደሚለዋውጡ አይተናል።
  2. ኡርጃዊ ዕለቶችን አንድ ዓመት ሙሉ በመለካትና አማካያቸውን (average, mean) በመፈለግ የሚገኘው እሴት አማካይ ኡርጃዊ ዕለት (mean sidereal day) ይባላል። 
  3. በተመሳሳይ መንገድ ጀንበራዊ ዕለቶችን አንድ ዓመት ሙሉ በመለካትና አማካያቸውን (average) በመፈለግ የሚገኘው እሴት አማካይ ጀንበራዊ ዕለት (mean solar day) ይባላል።  

solar day = ጀንበራዊ ዕለት
mean solar day = አማካይ ጀንበራዊ ዕለት
sidereal day = ኡርጃዊ ዕለት
mean sidereal day = አማካይ ኡርጃዊ ዕለት

የኑሲቃ ብያኔ (Definition of the Second)

  1. ከ1949 ዓ.ም በፊት የጊዜ ደርክ (standard of time) ተበይኖ (defined) የነበረው አማካይ ጀንበራዊ ዕለትን (mean solar day) መሠረት በማድረግ ነበር።
  2. በዚህ ብያኔ (definition) መሠረት አማካይ ጀንበራዊ ዕለት (mean solar day) ለ 86, 400 ሽንሽኖች ተሸንሽኖ አንዱ ሽንሽን 1 ኑሲቃ (1 second) ነው ተብሎ ነበር። 
  3. በሌላ አባባል አማካይ ጀንበራዊ ዕለት (mean solar day) ማለት እቅጩን (exactly) 86,400 ኑሲቃ (86,400 second) ወይም 1,440 ደቂቃ (1,440 minute) ወይም 24 ሰዓት (24 hours) ማለት ነው ተብሎ ተበይኖ (defined) ነበር።
    • ነገር ግን ያማካይ ጀንበራዊ ዕለት ርዝመት (length of mean solar day) ቋሚ (constant) ሳይሆን በተለያዩ ምክኒያቶች ካመት ዓመት የሚጨምር መሆኑ ተደረሰበት። 
    • ከነዚህም ምክኒያቶች አንዱና ዋናው በውቅያኖሶች ውሃ እና በደረቅ ምድር መካከል ያለው ማዕበላዊ ሰበቃ (tidal friction) ነው። 
    • ይህም ማዕበላዊ ሰበቃ (tidal friction) ያማካይ ጀንበራዊ ዕለትን ርዝመት የሚጨምረው ምድር በረቲዷ (axis) ላይ የምትሾርበትን (spin) ፍጥነት (speed) በመቀነሰ ነው፣ የሰበቃ (friction) አንደኛው ጦሱ (effect) ፍጥነትን (speed) መቀነስ ነውና።
    • ማዕበላዊ ሰበቃ (tidal friction) ያማካይ ጀንበራዊ ዕለትን ርዝመት (length) በየመቶ ዓመቱ  (every hundred years) በቅርበዛ (approximately) 2 ኑሲቃ (2 seconds) ገደማ ይጨምረዋል። 
  4. በዚህም ምክኒያት ሰገለኛወች (scientists) ካማካይ ጀንበራዊ ዕለት (mean solar day) የበለጠ እቅጭነትን (accuracy) እና ተራቢነት (reproducibility) ያለው የጊዜ ደርክ (standard of time) መበየኛ (define) ክስተት (phenomenon) መፈለጋቸውን ቀጠሉ።
  5. ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ካማካይ ጀንበራዊ ዕለት (mean solar day) እጅግ በተሻለ ሁኔታ የጊዜን ደርክ (standard of time) ለመበየን (define) የሚያስችል በሲዝየም-133  (cesium-133) ቀኒጥ (atom) ላይ የተመሠረተ ቀኒጣዊ ቃቢሳ (atomic clock) ተፈለሰፈ። 
  6. ይህም ቀኒጣዊ ቃቢሳ (atomic clock) በሲዝየም-133 ቀኒጥ (cesium-133 atom) ውስጥ የሚገኙ ተልኑሶች (electrons) ካንድ የተወሰነ ከፍተኛ የጉልበት ጠለል (one specific higher energy level) ተነስተው ወደ ሌላ የተወሰነ ዝቅተኛ የጉልበት ጠለል (another specifice lower energy level)  ሲወርዱ የሚያመነጩት ጨዳሚ ሞገድ (radio wave) ያለውን ዝውተራ (frequency) በከፍተኛ ጭሃነት (high precision) መለካት የሚችል ቃቢሳ ነው። 
  7. በዚህም ምክኒያት በ1960 ዓ.ም ላይ የጊዜ ቶካድ (unit of time) ማለትም ኑሲቃ (second) የሲዝየም-133 ቀኒጥ (cesium-133 atom) ሚያመነጨው ጨዳሚ ሞገድ (radio wave) ካለው ዝውተራ (frequency) አንጻር እንደሚከተለው ተበየነ (defined)።

ብያኔ (definition)፤ አንድ ኑሲቃ (one second) ማለት ከሲዝየም-133 ቀኒጥ (cesium-133 atom) የሚመነጭ ጨዳሚ ሞገድ (radio wave) 9,192,631,770 ኡደቶችን (cycles)  ለማጠናቀቅ የሚፈጅበት ጊዜ ማለት ነው።

  1. ዘመናዊው የሲዝየም-133 (cesium-133) ቀኒጣዊ ቃቢሳ (atomic clock) እጅግ ከፍተኛ እቅጭነት (very high accuracy) ያለው ቃቢሳ (clock) ከመሆኑ የተነሳ በ 20 ካልጃኖ ዓመታት (20 million years) ውስጥ የሚስተው 1 ኑሲቃ (one second) ብቻ ነው።
  2. በቀኒጣዊ ቃቢሳ (atomic clock) ላይ በተመሠረተው በዘመናዊው የኑሲቃ ብያኔ (definition of the second) መሠረት በየመቶ ዓመቱ (every hundred years) በ 2 ኑሲቃ (2 seconds) ገደማ የሚጨመረው ያማካይ ጀንበራዊ ዕለት (mean solar day) ርዝመት ባሁኑ ዘመን ያለው እሴት በቅርበዛ (approximately) 86, 400.002 ኑሲቃ ነው። 

መስፍን አረጋ
mesfinamharic.com
mesfin.arega@gmail.com