Physical Address
304 North Cardinal St.
Dorchester Center, MA 02124
Physical Address
304 North Cardinal St.
Dorchester Center, MA 02124

መስፍን አረጋ
ፊልጡፍ፣ ኋልጡፍ፣ ላዕልጡፍ፣ ታሕትጡፍ
አብዛኛውን ጊዜ ቃሎች የሚመሠረቱት ፊልጡፍ (prefix) እና/ወይም ኋልጡፍ (suffix) በመጠቀም ነው። ፊልጡፍ ማለት ከቃል ፊትጌ (በስተፊት) የሚለጠፍ ማለት ሲሆን፣ ኋልጡፍ ማለት ደግሞ ከቃል ኋልጌ (በስተኋላ) የሚለጠፍ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ስነምግባር በሚለው ቃል ላይ ስነ ፊልጡፍ ሲሆን፣ ደንታቢስ በሚለው ቃል ላይ ደግሞ ቢስ ኋልጡፍ ነው።
ፈልጡፍ እና ኃልጡፍ በተንዛዛ አጠራር ባዕድ መነሻ እና ባዕድ መድረሻ የምንላቸው ናቸው። ፊልጡፍ የሚለው ቃል የተመሠረተው፣ ፊት እና ልጡፍ የሚሉትን ቃሎች በማጣመር ሲሆን፣ ኋልጡፍ የሚለው ቃል የተመሠረተው ደግሞ ኋላ እና ልጡፍ የሚሉትን ቃሎች በማጣመር ነው።
በተመሳሳይ መንገድ ላዕልጡፍ (superscript) ማለት ከቃል ወይም ከቁጥር ራስጌ የሚጻፍ ጽሑፍ ማለት ሲሆን፣ ታሕትጡፍ (subscript) ማለት ደግሞ ከቃል ወይም ከቁጥር ግርጌ የሚጻፍ ጽሑፍ ማለት ነው። ላዕል (super-) እና ታሕት (sub-) የሚሉት ፊልጡፎች (prefixes) የተገኙት ደግሞ ላዕላይ እና ታሕታይ ከሚሉት የግእዝ ቃሎች ነው።
ፊልጡፍ፣ ኋልጡፍ፣ ላዕልጡፍ፣ እና ታሕትጡፍ በወል (ማለትም ባጠቃላይ) ስም ሲጠሩ ልጡፍ ይባላሉ። በሌላ አባባል ልጡፍ የሚለው ቃል ከአራቱ ቃሎች (ፊልጡፍ፣ ኋልጡፍ፣ ላዕልጡፍ እና ታሕጡፍ) ውስጥ አንዱን፣ የተወሰኑትን ወይም ደግሞ ሁሉንም ይወክላል ማለት ነው።
prefix – ፊልጡፍ
suffix – ኋልጡፍ
superscript – ላዕልጡፍ
subscript – ታሕትጡፍ
ራስጌሻ፣ ግርጌሻ፣ ራስጌራግ፣ ግርጌራግ
ራስጌ እና ግርጌ የሚሉትን ቃሎች ማስታወሻ ከሚለው ቃል ጋር በማጣመር ራስጌሻ (hearnote)፣ ግርጌሻ (footnote) የሚሉትን ቃሎች እናገኛልን። ራስጌሻ ማለት ከገጽ ራስጌ የሚጻፍ ማስታወሻ ማለት ሲሆን፣ ግርጌሻ ማለት ደግሞ ከገጽ ግርጌ የሚጻፍ ማስታወሻ ማለት ነው።
በተመሳሳይ መንገድ ራስጌ እና ግርጌ የሚሉትን ቃሎች ሐረግ (phrase) ከሚለው ቃል ጋር በማጣመር ራስጌራግ (header) እና ግርጌራግ (footer) የሚሉትን ቃሎች እናገኛልን። ራስጌራግ ማለት ከገጽ ራስጌ የሚጻፍ ሐረግ (የራስጌ ሐረግ) ማለት ሲሆን፣ ግርጌራግ ማለት ደግሞ ከገጽ ግርጌ የሚጻፍ ሐረግ ማለት ነው።
headnote – ራስጌሻ
footnote – ግርጌሻ
header – ራስጌራግ
footer – ግርጌራግ
መስፍን አረጋ
mesfinarega.com
mesfinamharic.com
mesfin.arega@gmail.com