Physical Address
304 North Cardinal St.
Dorchester Center, MA 02124
Physical Address
304 North Cardinal St.
Dorchester Center, MA 02124

መስፍን አረጋ
መጥረቢያ መስሎ ስለታም፣ ብርቱ ሲመስለኝ ከቀለም
ፊደል ከፊደል ሲታገሉ፣ ወገን አሸነፈ አሉ።
አለቃ ተገኝ ታምሩ ( ያማረኛ ሐረግ በቅኔወች ሕግ፣ ገጽ 22)
ያማረኛ ፊደሎች እያንዳንዳቸው የየራሳቸው መጠርያ ስም አላቸው። እነዚህም ያማረኛ ፊደሎች መጠርያ ስሞች “ዐዲስ ያማረኛ መዝገበ ቃላት” በተሰኘው በታላቁ ሊቅ ባለቃ ደስታ ተክለወልድ ቃልመዝ (dictionary) ውስጥ ገጽ 10 ላይ ተዘርዝረዋል። እኔም መስፍን አረጋ እነዚህን ያማረኛ ፊደሎች ስሞች መሠረት አድርጌ በትንሹ በመለወጥ ለማስታወስ የሚቀሉ፣ ላጠራርና ላረባብ የሚያመቹ፣ ስርዓትን የተከተሉ አዳዲስ ስሞችን ላማረኛ ፊደሎች አውጥቸላቸዋለሁ። እነዚህም ስሞች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።
ፊደል የፊደል ስም
ሀ ሃሌፍ
ለ ላሌፍ
ሐ ሓሜፍ
መ ማሌፍ
ሠ ሣሌፍ
ረ ራሌፍ
ሰ ሳቴፍ
ሸ ሻሌፍ
ቀ ቃሌፍ
በ ባሌፍ
ተ ታሌፍ
ቸ ቻሌፍ
ኀ ኃሬፍ
ነ ናሌፍ
ኘ ኛሌፍ
አ አሌፍ
ከ ካሌፍ
ኸ ኻኬፍ
ወ ዋሌፍ
ዐ ዐቴፍ
ዘ ዛሌፍ
ዠ ዣሌፍ
የ ያሌፍ
ደ ዳሌፍ
ጅ ጃሌፍ
ገ ጋሌፍ
ጠ ጣሌፍ
ጨ ጫሌፍ
ጰ ጳሌፍ
ጸ ጻዴፍ
ፀ ፃየፍ
ፈ ፋሌፍ
ፐ ፓሌፍ
ሐሜፍ የሚለው የፊደል ሐ ስም የሐመርን ሚስጥር ያመለክታል፣ ሐመር ማለት በግእዝ ማለት ነውና። ኃሬፍ የሚለው የፊደል ኀ ስም ደግሞ የመመረጥን ሚስጥር ያመለክታል፣ ኀረየ ማለት በግእዝ መረጠ ማለት ነውና። ጻዴፍ የሚለው የፊደል ጸ ስም ጸደይን ሲያመለክት፣ ፃየፍ የሚለው የፊደል ፀ ስም ደግሞ ፀሐይን ያመለክታል። እነዚህ የፊደል ስሞች በመጠቀም የሚከተሉትን የመሳሰሉ ቃሎች እናገኛለን።
alpha particle = አሌፍ እኑስ (አሌፍኑስ)
alpha ray = አሌፍ ጨረረ
beta particle = ባሌፍ እኑስ (ባሌፍኑስ)
beta ray = ባሌፍ ጨረር
gamma particle = ጋሌፍ እኑስ (ጋሌፍኑስ)
gamma ray = ጋሌፍ ጨረር
አልፋና ኦሜጋ
አልፋና ኦሜጋ (alpha and omega) የሚለው መጀመርያንና መጨረሻን የሚያመለክት ሐረግ የተመሠረተው የግሪክ ፊደሎችን ተራ መሠረት በማድረግ ባንደኛውና በመጨረሻው የግሪክ ፊደሎች ስም ነው። ስለዚህም በሀለሐመ የፊደል ተራ አካሄድ የአልፋና ኦሜጋ ያማረኛ ትርጉም ሃሌፍና ፓሌፍ ይሆናል። በአበገደ የፊደል ተራ አካሄድን ከሄድን ደግሞ የአልፋና ኦሜጋ የአማረኛ ትርጉም አሌፍና ጃሌፍ ይሆናል።
alpha and omega = ሃሌፍና ፓሌፍ (በሀለሐመ አካሄድ)
alpha and omega = አሌፍና ጃሌፍ (በአበገደ አካሄድ)
የፊደል ተራ
የፈደል ተራ ከአበገደ ወደ ሀለሐመ የተለወጠው ከፍሬምናጦስ (ከሣቴ ብርሃን ሰላማ) ወዲህ ነው። ብርሃን ገላጭ (ከሣቴ ብርሃን ማለት ብርሃን ገላጭ ማለት ነው) የሚባሉት እነ ከሣቴ ብርሃን አበገደን ወደ ሀለሐመ የለወጡት ደግሞ የራሳቸውን የግሪከን ፊደል አልፋ፣ ቤታ፣ ጋማ የነበረውን ፩ ፣ ፪ ፣ ፫ እያሉ በግእዝ ፊደል ላይ አሃዝ (ቁጥር) አድርጎ ለማስገባት እንዲመቻቸው ነበር። ይህም ሥራቸው የግእዝን ፊደሎች ከሴም ቋንቋወች ደንብ እንዲያፈነግጡ አድርጓቸዋል። ለተጨማሪ ማብራርያ “መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ዐዲስ” የሚለውን የታላቁን ሊቅ ያለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን መጽሐፍ (ገጽ 32) መመልከት ይቻላል።
ምንም እንኳን አቡጊዳ ሲመለከቱት ዝብርቅርቅ ቢመስልም፣ የፊደሎቹ አደራደር ግን ስርዓትን የተከተለ ነው። የመጀመርያው ዐምድ ግእዝ ነው፣ ማለትም በመጀመርያው ዐምድ ላይ የሚገኙት ሁሉም ፊደሎች (አበገደ) ግእዞች ናቸው። በተመሳሳይ ሁኔታ የሁለተኛው ዐምድ ፊደሎች ካዕብ፣ የሦስተኛው ዐምድ ፊደሎች ሣልስ፣ ያራተኛው ዐምድ ፊደሎች ራብዕ፣ ያምስተኛው ዐምድ ፊደሎች ሓምስ፣ የስድስተኛው ዐምድ ፊደሎች ሳደስ፣ የሰባተኛው ዐምድ ፊደሎች ደግሞ ሳብዕ ናቸው።
በተጨማሪ ደግሞ በአበገደ ተራ ውስጥ የእያንዳንዱ ፊደል ግእዝ፣ ካዕብ፣ ሣልስ፣ ራብዕ፣ ሓምስ፣ ሳድስና ሳብዕ ወደቀኝ በሚያቀና ቀጥታ መስመር ላይ የተደረደሩ ናቸው። ለምሳሌ ያህል ፊደል ዘ በአበገደ ተራ ሲደረደረ ዘ፣ ዙ፣ ዚ፣ ዛ፣ ዜ፣ ዝ፣ ዞ እያለ በቀጥታ መስመር ላይ ወደቀኝ ያሻቅባል፣ ማለትም ወደቀኝ (ወደ የማን) እና ወደ ሰማይ (ወደ ራማ) ያመለክታል። ለዚህ ነው እንግዲህ፣ የግእዝ ፊደሎች ውብ ከመሆናቸውም በላይ ራማዊ (ሰማያዊ) ናቸው የሚባለው፣ ወነበረ በየማነ አበሁ (ባባቱ ቀኝ ተቀመጠ) እንዱሉ።
አ ቡ ጊ ዳ ሄ ው ዞ
በ ጉ ዲ ሃ ዌ ዝ ዦ
ገ ዱ ሂ ዋ ዜ ዥ ሖ
ደ ሁ ዊ ዛ ዤ ሕ ጦ
ሀ ው ዚ ዣ ሔ ጥ ጮ
ወ ዙ ዢ ሓ ጤ ጭ ዮ
ዘ ዡ ሒ ጣ ጬ ይ ኮ
ከአቡጊዳ የፊደል ተራ የምንረዳው ትልቁ ቁምነገር አብናቶቻችን (ማለትም አባቶቻችን እና እናቶቻችን) ማናቸውንም ነገር የሚሠሩት የዘፈቀደ ሳይሆን፣ አውጥተውና አውርደው፣ አስበውና አሰላስለው መሆኑን ነው።
ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ እንዳስገነዘቡት (‘መጽሐፈ ሰወሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ዐዲስ” ግጽ 10) ባለም ላይ ያሉ ቋንቋወች ሁሉ በባልተቤታቸው ሲጠሩ ፣ አማረኛ ባማሮች፣ ትግረኛ በትግሬወች፣ እንግሊዘኛ በንግሊዞች፣ ግእዝ ግን በማንም ነገድ ስም አልተጠራም፣ በቀዳማይ ቋንቋነቱ እንጅ፣ ግእዝ ማለት አንደኛ፣ የመጀመርያ ማለት ነውና፣ ሀ ግእዝ እንዲሉ፣ የመጀመርያው ሀ ሊሉ።
አገራችን ቅድስት ጦቢያ የሰው ልጅ ምንጭነቷ በሰገል (science) የተረጋገጠ መሆኑን ይዘን፣ ዓለም ሁሉ ባንድ ቋንቋና ባንድ ንግግር ነበረች (“ወኮነ ሁሉ ምድር አሐተ ከንፈረ ወአሐደ ነገረ”፣ ዘፍጥረት 1፡11) የሚለውን ስንጨምርበት ደግሞ የአዳም (ማለትም የመጀመርያው የሰው ልጅ) ቋንቋ ግእዝ ነበር በማለት በድፍረት ልንናገር እንችላልን። የግእዝን ቀዳማይ ቋንቋነት ደግሞ የተለያዩ እውቅ የመዱስ (bible) ምሁራን፣ በተለይም ደግሞ የመጀመርያውን የግእዝ ቃልመዝ (dictionary) የቀለመዘውን ኦጊስቲን ዲልማንን (Augstin Dillman) ጨምሮ አያሌ የዶሽጌ (Deutschland, Germany) ሊቃውንት መስክረውለታል።
ጦቢያ ስለሆነ ቀዳሚ የሰው ዘር
ሰውን በአምሳሉ መፍጠሩን ሲናገር
ጌታ ማለቱ ነው ነኝ እንደሱ ጥቁር።
ስለዚህም ሰይጣን የጌታ ባላንጣ
በተቃራኒ መልክ ይሆናል የነጣ።
ለፈረንጅ ስዕል የሚሰግድ ሐበሻ
ተዋርዶ አዋራጅ የረከሰ ውሻ።
ያው ድምጽ ፊደሎች
ባማረኛ ቋንቋ ተናጋሪወች ዘንድ ፌደሎች አ፣ዐ፣ ሀ፣ ሐ፣ ኀ፣ ሰ፣ ሠ፣ ጸ፣ ፀ አንድ ዓይነት ድምጽ ያላቸው ፊደሎች ናቸው። እነዚህን አንድ ዓይነት ድምጽ ያላቸው ፊደሎች በተመለከተ ባንዱ ፊደል /መጻፍ/ ያለበትን በሌላ ፊደል መጻፍ ትርጉሙን ሊቀይረው ይችላል። ለምሳሌ ያህል መሀረ ማለት አስተማረ ማለት ሲሆን፣ መሐረ ማለት ደግሞ ይቅር አለ ማለት ነው። ስለዚህም ትምህርት እንጅ ትምሕርት ተብሎ አይጻፍም። በተመሳሳይ ሁኔታ ሠረቀ ማለት ወጣ፣ ብቅ አለ ማለት ሲሆን፣ ሰረቀ ማለት ደግሞ ሌብነት ፈጸመ ማለት ነው። ስለዚህም ምሥራቅ እንጅ ምስራቅ ብሎ መጻፍ፣ እንዲሁም ሠረቀ ብርሃን እንጅ ሰረቀ ብርሃን ብሎ መጻፍ ትክክል አይደለም።
ያንዱ ፊደል ሥራ በሌላው ሲሠራ
የጸሐፊ ደዌ፣ ያታሚ መከራ።
ይህ ማለት እንግዲህ፣ ማናቸውም ጸሐፊ ትክክለኛወቹን ፊደሎች ለመጠቀም የሚቻለውን ያህል መጣር አለበት ማለት ነው፣ ምንም እንኳን “ፊደልና ሽንፊላ ቢያጥቡት አይጠራም” እንደሚባለው ስህተት የመሥራቱ ዕድል ሁልጊዜ ያለ ቢሆንም። ይሄው እኔም ስሕተትን ስህተት ብየ በመጻፍ እዚሁ በዚሁ ተሳሳትኩ።
መስፍን አረጋ
mesfinarega.com
mesfinamharic.com
mesfin.arega@gmail.com