Physical Address
304 North Cardinal St.
Dorchester Center, MA 02124
Physical Address
304 North Cardinal St.
Dorchester Center, MA 02124

መስፍን አረጋ
የራሱን ንጹሕ ጥበቆ፣ ራሱ ጥሎ አውልቆ
የሰው ቆሻሻ አጥልቆ፣ ተበክሎ ተጨመላልቆ፣
ሰው ተጸይፎት ርቆ፣ ሲሳለቅበት በሽቆ
ዙሮ እንባ ፈንጥቆ፣ እያለቀሰ ተነፋርቆ
ተናኩኝ ይላል ተንሰቅስቆ፣ ራሱን በራሱ አስንቆ።
ተግዳሮት የሚለውን ቃል ለማርባት ይመች ዘንድ ገዲር (challenge) እንለዋለን። ግሱም ሲረባ ገደረ (to challenge)፣ ግድር፣ ግዱር (challenged)፣ ገዳሪ (challenger)፣ ግደራ፣ ግድረት፣ ግዳሬ፣ ግዳሮሽ (challenging) እያለ ይሄዳል። ስለዚህም ያማረኛ ገዲሮች ማለት ያማረኛ ተግዳሮቶች ማለት ነው። የዚህ ጦማር ዓላማም ስላማረኛ ገዲሮች ማውሳት ነው።
አማረኛችን በባዕድ ቋንቋወች በተለይም ደግሞ በእንግሊዘኛና በመጠኑም ቢሆን ሐይማኖትን አስታኮ በዐረብኛ ክፉኛ እየተጠቃ ይገኛል፡፡ ይህ እንግሊዘኛ የሚባል ትናንት የተፈጠረ፣ እዚህ ግባ ይባል ያልነበረ መናኛ ቋንቋ፣ ዛሬ ከግሪክ፣ ከላቲን፣ ከሕንድ ወዘተ. አግበስብሶ በመለቃቀም ባከማቸው ሠራዊቱ ተጠናክሮ፣ ጎልብቶና አይሎ በመምጣት አማረኛን ሊደመስሰው፣ ከምድረገጽ ሊያስወግደው፣ ድምጥማጡን ሊያጠፋው፣ በገዛ ቤቱ ውስጥ እያባረረው፣ እያሳደደው፣ እያራወጠውና፣ እያሽመደመደው ይገኛል፡፡
ባያስደንቅም እንኳን እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ባገራችን በቅድስት ጦቢያ ላይ የዘመተው የእንግሊዘኛ ሠራዊት የጦር አበጋዞችና ጋሻጃግሬወች የራሷ የጦቢያ ጉዶች፣ ምሁር ተብየወችና ባለስልጣኖች፣ አባቱን አያውቅ አያቱን ናፈቅ ጥራዝ ነጠቆች፣ በሰው ወርቅ ልድመቅ ባዮች መሆናቸው ነው፡፡ መሠሪ ስልታቸውም በእንግለዘኛ ካልተናገሩ እንደሚያስንቅ፣ ካልተሰየሙ እንደሚያሳፍር፣ ካልተማሩ እንደማይሰለጠን፣ ካልጸለዩ ጸሎት እንደማይሰምር መደዴውን ሕዝብ በማሳመን የራሱን ቋንቋ እራሱ እንዲገድል፣ ቀኝ እጁን በግራ እጁ ቆርጦ እንዲጥል ማድረግ ነው፡፡ አማረኛ መውለድና መዋለድ፣ መርባትና መራባት፣ መስፋትና መስፋፋት የማይችል መኻን፣ አይቀሬ ዕጣውም እያረጀና እያፈጀ ሂዶ መክሰም – መሞት – እንደሆነ በመስበክ ያማረኛን ተከላካይ ጦር በወሬ መፍታት – መበታተን – ነው፡፡
መከራ ደግሞ የሚያጠቃው በጋራ ነውና፣ ያማረኛ ተከላካይ ጦር ታላላቅ መሪወቹን፣ ጠቅሎቹንና፣ ፊታውራሪወቹን እነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌን፣ እነ አለቃ ደስታ ተክለወልድን፣ እነ አለቃ ከበደ ሚካኤልን በሞት በመነጠቁና በነሱ እግር የተተኩ የቋንቋ አበጋዞችን ባለማግኘቱ፣ ያላንዳች መፈናፈኛ ዙርያውን በጠላት ተከቦ፣ በሰርጎ ገቦች ተወጥሮ፣ ከበባውን የሚበረግድለት፣ ውጥረቱን የሚያረግብለት ደጀን እንዲላክለት እሪ፣ ኡኡ ቢል ሰሚ አጥቶ፣ ስንቁና ትጥቁ ወደ ማለቁ ተቃርቦ፣ እጅግ ተዳክሞ፣ ተስፋ ቆርጦ፣ የሞት ሞቱን እየተንገታገተ ይገኛል፡፡
ይህ በመሪ እጦት ቅጥ አጥቶ የተበታተነ ያማረኛ ጦር ባጭር ጊዜ ውስጥ ካልተሰባሰበና በስርዓት ካልተመራ፣ የመከላከያ ወረዳውን ካላጠናከረና ማኻሉን ከሰርጎ ገቦች ካላጸዳ፣ ወራሪን መክቶ ድባቅ የሚመታበት፣ ሰርጎ ገብን ለይቶ የሚመነጥርበት ዘመናዊ መሣርያ ካልታጠቀ፣ የጠላትን አሰላለፍ የሚያጤን፣ የሰርጎ ገብን ሚና የሚያጠና፣ በዓላማው የጸና፣ በማንነቱ የሚተማመን፣ ለማንም ለምንም የማይበገር ፈጣን፣ ሳተና ጦር ካላዘጋጀና፣ ካላደራጀ፣ ከወንድሞቹ ከኦሮምኛ፣ ከወላይትኛ፣ ከሲዳምኛ፣ ከትግርኛ ጦሮች ጋር ሕብረት ካልፈጠረ፣ ያባቱን የግእዝን ጦር የውጊያ ስልት ካልገበረተ፣ ሙሉ በሙሉ የሚሸነፍበት፣ ነጭ ዐልማቅ እያውለበለበ፣ አጁን ሰጥቶ፣ ተማርኮ ወደ ግዞት፣ ቀጥሎም ወደ ግብአተ መሬት የሚላክበት አሳፈሪ፣ አስፈሪ ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ አማረኛ ሲሸነፍ፣ አማረኛ አማረኛነቱን ሲያቆም፣ እንዳበጁት መበጀቱ የተነገረለት ድንቅ ቋንቋ ተበለሻሽቶ ሲቀር፣ የኛም ማንነት ካማረኛ ጋር አብሮ ያከትማል፣ ቋንቋ ማንነት ነውና፡፡
አልፍ አእላፍ አብናቶቻችን የማንነታቸው መግለጫ የሆነውን ቋንቋቸውን ለማስከበር መልዕሉን መስዋእትነት እንዳልከፈሉ ሁሉ፣ ያሣ ግማቱ ካናቱ ነውና፣ ዛሬ በገዛ አገራቸው ላይ የገዛ ቋንቋቸውን የሚናገሩ ሕጻናቶች አይቀጡ ቅጣት ከሚቀጡበት፣ አማረኛ መናገርን ዲንጋ ከመወረወር የሚቆጥሩ ‹‹ትምህርት ቤቶች›› እንደ አሸን ከፈሉበት፣ ባማረኛ መዋረድ የሚኮሩ ናላዊ አመንዝራወች (mental prostitutes) ከነገሡበት፣ እግራቸው ስለጠነከረ አይምሯቸው የዳበረ፣ ደረታቸው ስላበጠ ዓይናቸው የተገለጠ፣ ኪሳቸው ስለተነፋ አስተሳሰባቸው የሰፋ የሚመስላቸው እንጭጮች ከሚታበዩበት፣ አሰቃቂ፣ ሰቅጣጭ ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
የሰው ስሞች ሰፎንያስ፣ ጎዶልያስ፣ አብዱልከሪም፣ አቡቦከር …የድርጅት ስሞች ኩርፍቱ ሪዞርት፣ ቸርችል ሆቴል፣ ዳውንታውን ካፌ፣ ኒውዮርክ ሬስቶራንት …የሕንፃ ስሞች ፍሬንድሽፕ ሕንጻ፣ ሌክስ ፕላዛ፣ ምንትሴ ቢልዲንግ፣ ቅብጥርሴ ታወር …የሸቀጥ ስሞች ሃይላንድ ውሃ፣ ፋንታስቲክ ሳሙና፣ ሂፖፕ ኬክ፣ ሴንሴሽን ኮንዶም …የሕግ አስከባሪ ማዕረጎች ሳጅን፣ ኢንስፔክተር፣ ኮማንደር፣ ሱፐርቫይዘር …ስካይ ባስ፣ ፕሬሚያር ሊግ፣ ዲስትሪክት፣ ኤጀንሲ …ስኩል ኦፍ ቱሞሮ፣ ፕሪስቴጅየስ ዩዝ አካዳሚ …ሪቨር ኦፍ ላይ ቸርች … ‹‹ፓስተሩ ምርጥ ነው፣ ካማረኛ ይልቅ በንግሊዘኛ መስበክ ይቀናዋል›› …. ‹‹የኔ ልጅ እጹብ ናት፣ የምታልመው እንኳን በንግሊዘኛ ነው›› …ኧረ ምኑ ቅጡ ….
ጉዱ ተዘርዝሮ መቸ ይዘለቃል
እንደው በደፈናው በጥቅል ባጭር ቃል
ጭምልቅልቅ ብሏል ማለቱ ይበቃል፡፡
ታላቁ ጦቢያዊ ሊቅ አለቃ ኪደነወልድ ክፍሌ ‘’መጽሐፍ ሰወሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ዐዲስ’’ በተሰኘው ታላቁ መጽሐፋቸው መግቢያ ላይ (ገጽ 10) አበክረው እንዳስገነዘቡ “ቋንቋና ቋንቋ መወራረሳቸው ያለ፣ የነበረና የሚኖረ ቢሆንም፣ የራስን እየጣሉ የባዕድን መውሰድ ግን ዝሙትነት ነው’’ – ሚስቱን እቤቱ አስቀምጦ ከሌላ ሴት ጋር የሚማግጥ ሰው ዘሟች እንደሆነ ሁሉ። እኒህ ታላቅ ጦቢያዊ ከሰባና ሰማኒያ ዓመታት በፊት ባማረኛ ላይ የደረሰውን ብክለት ለመግልጽ ዝሙት የሚለውን ቃል ከተጠቀሙ፣ የዛሬውን ቢያዩ ምን ይሉ እንደነበር ግምቱ ላንባቢ ትቸዋለሁ።
እንግዲህ በዘጋቢ ፋንታ ሪፖርተር፣ በወደብ ፋንታ ፖርት፣ በርቱዕ ፋንታ ኦርቶዶክስ፣ በአቡን ፋንታ ጳጳስ፣ በመሮጦል ፋንታ ካቴድራል፣ በሸንጎ ፋንታ ፓርላማ፣ በቀጠና ፋንታ ዞን ስንጠቀም ሌላ ምንም ሳንሆን ዘሟቾች – የራሳችን አሮብን የሰውን የምናማስል ከንቱወች – ነን ማለት ነው። እጅግ ሲበዛ ዘሟቾች ከመሆናችን የተነሳ፣ አገራችንን ጦቢያን እንደፈረንጆቹ ኢትዮፕያ፣ አህጉራችንን አፍሪቃን ደግሞ እንደ ፈረንጆቹ አፍሪካ እስከማለት ደርሰናል።
ያማረኛ ጠላቶች የሆኑትን የወያኔንና የኦነግን መንግስታትና ልሂቃን ወደጎን ትተን፣ አገረወዳድ ነን ይሉ የነበሩት ያገራችን መንግስታተና ልሂቃን ተገቢውን ትኩረት ላማረኛ ሰጥተውት ቢሆን ኖሮ፣ ባሁኑ ሰዓት የሚታየው ዓይን የሚያቆስል አጸያፊ ብክለትና ጉራማይሌ ባልተከሰተ ነበር። ሆኖም ግን ላለፈው ክረምት ቤት /አይሰራምና/፣ ያዳም ቋንቋ የግእዝ ትልቁ ልጅ አማረኛ በአሕዛብ ቋንቋ ከመቆሸሽ አልፎ ሲጨማለቅ ማየት አንጀታችንን የሚያሳርረን፣ ልባችንን የሚያደማን ጦቢያውያን ሁሉ የቆሸሸውን በማጽዳት፣ የተሳሳተውን በማረም፣ የተዘበራረቀውን በማደራጀትና የሌለውን በመፍጠር አማረኛን ከወደቀበት አንስተን ወደሚገባው ልዕልና ከፍ ለማድረግ በቁጭት መንፈስና በነቂስ መረባረብ አለብን።
አማርኛ፣ ማናቸውንም ነገር በቀላሉ ለመገለጽ የሚያስችል እጅግ በጣም ቀና፣ ቅን፣ ተጣጣፊና፣ በዚያ ላይ ደግሞ ውብ ቋንቋ ነው፡፡ ዐበይት ከሚባሉት ከማናቸው የዓለም ቋንቋወች ጋር አቻ ለመሆን ብቻ ሳይሆን በብዙ እጥፍ በልጦ ለማስከንዳት የሚያስፈልገው የቆሸሸውን አጽድቶ፣ የተሳሳተውን አርሞ፣ የተዘበራረቀውን አደራጅቶ ቋንቋውን ስርዓት ማስያዝና አስፈላጊወቹን አዳዲስ ቃሎች መፍጠር ብቻና ብቻ ነው፡፡ እነዚህን ለማከናወን ደግሞ በቀላሉ የሚያስችሉን ከሰባ ስምነት የማያንሱ አገራዊ ቋንቋወች፣ ተቀድተው የማይልቁ የቃላት ምንጮች አሉን፡፡ ሁሉ በጃችን በደጃችን ነው፡፡ በነዚህ አገራዊ ቋንቃወች ላይ አማረኛ እንደ ልብ ለመተጣጠፍ ያለውን ወደር የለሽ ችሎታ ስንጨምርበት ደግሞ ወሰናችን ሰማይ ብቻ ይሆናል፡፡ አማረኛን በባዕዳን ቃሎች ከማኩሰስ በወገኖቹ ቃሎች ስናገዝፈው ደግሞ ሕዝባችን የበለጠ ላማፋቀርና ለማስተሳሰር የበኩሉን ጉልህ አስተዋጽኦ ያደርጋል፣ ቋንቋው የሁሉም ጦቢያውያን ገንዘብ ይሆናልና፡፡
አማረኛን ከግእዝ ጋር ሰልቆና አቡክቶ እንጀራ በመጋገር፣ በኦሮምኛ፣ በወላይተኛ፣ ሲዳምኛና ሌሎች ጦቢያዊ ቋንቋወች የተቀመመ ግሩም ወጥ በመሥራት፣ ወደር የማይገኝለት፣ ቢበሉት የማይጠገብ፣ እጅ የሚያስቆረጥም፣ በቀላሉ የሚላመጥና በጨጓራ የሚፈጭ፣ ለጤና ተስማሚ የሆነ፣ አስገስቶ፣ ደስ አሰኝቶ፣ ራስን የሚያስወድድ፣ በማንነነትና በምንነት የሚያኮራ እጹብ ድንቅ ምግብ መሥራት ይቻላል።
ታዋቂው ቱልቸኛ ሃይሌ ገብረሥላሴ እንዳለው፣ የማይቻል የለም – ሁሉም ይቻላል።
በራስህ ተማመን፣ ራስህን አክብር፣ በማንነትህና በምንነትህ ኩራ፣ የራስህን ውደድ፣ ጠንክረህ ሥራ፣ ፈጣሪ ካንተ ጋር ይሆናል፣ አገርህም እንደገና ትገናለች፣ የተነጠቀችውን የክብር ዙፋን ታስመልሳለች፣ የማንም ዘመነኛ አሕዛብ፣ የተናነት መጤ ጉግማንጉግ፣ መሳቂያና መሳለቂያ መሆኗም ለሃቹ ያከትማል፡፡
ድል ስታደርግ በሁሉም መስክ ትደነቃለህ፡፡ አብሔር ቀርቦታል፣ እጁን ታጥቦ ሠርቶታል፣ ባርኮታል፣ ቀድሶታል፣ መርቆታል፣ ግዛ ብዛ ብሎታል ትባላለህ፡፡ ያንተ የሆነ ነገር ሁሉ ይከበራል፣ ምንም ያህል ተልካሻ ቢሆንም፡፡ የቀባጠርከው ሁሉ ከውነት ይቆጠራል፣ ውሸት፣ የውሸት ውሸት፣ ዓይን ያወጣ፣ ጥርስ ያገጠጠ ቅጥፈት ቢሆንም፡፡ ሌላው ሁሉ አንተን መሆን፣ አንተን መምሰል፣ ያንተን ማድረግ ይፈልጋል፣ የሱ የራሱ ያንተ ከሚባለው ሺ ጊዜ የሚያስንቅ ቢሆንም፡፡ ቆንጆ፣ ውብ ትባላለህ፣ ፊትህ እንደ ሶለግ የሾጠጠ፣ ቆዳህ እንደ ሊጥ የለጠለጠ፣ የነጨብክ የነጫጨብክ፣ ሲቀርቡህ አሙካ አሙካ የምትሸት፣ የገማህ የገለማህ ብትሆንም፡፡ ፈጣሪ በምሥልህ ተሥሎ፣ በየቤተሔሩ ተሰቅሎ ይሰገድልሃል፣ ሥራህ ሁሉ የሰይጣን ቢሆንም።
ድል ስትደረግ፣ በሰው እጅ ስትወድቅ፣ በሁሉም መስክ ትናቃለህ፡፡ አብሔር ርቆታል፣ አርክሶታል፣ አውግዞታል፣ ረግሞታል፣ ተጨቆን፣ ተገዛ ብሎታል ትባላለህ፡፡ ያንተ የሆነ ሁሉ ይናቃል፣ ምንም ያህል ግሩም ቢሆንም፡፡ የወደክ ግንድ ነህና ምሣር ይበዛብሃል። ሁሉም ባንተ ላይ ይረባረባል፣ መጥፎው ሁሉ ባንተ ይሳበባል፣ የእኩይ ሁሉ ምንጭ፣ የክፋት ሁሉ መንስዔ ትደረጋለህ፣ ማስጠሌ፣ ፉንጋ ትባላለህ። አር እንደነካው እንጨት ሁሉም ይጸየፍሃል። የሰይጣን ምልክት ትደረጋለህ።
ድልን የሚያጎናጽፈው ደግሞ የመሣርያ ብዛት ወይም ጥራት ሳይሆን፣ የመንፈስ ቆራጥነት ብቻና ብቻ ነው፡፡ ታላቁ ናፖሊዮን እንዳለው ’’ባለም ላይ ያሉት ኃይሎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ እነሱም ሰይፈና መንፈስ ናቸው፣ የመጨረሻው ድል ደግሞ ሁልጊዜም የመንፈስ ነው፡፡’’ ታሪክ ደጋግሞ የመሰከረው፣ አሁንም በገሃድ እየመሰከረ ያለውና፣ ወደፊትም ሁልጊዜም የሚመሰክረው ይሄን መሠረታዊ ሕቅ ብቻና ብቻ ነው፡፡ እሾህን በሾህ፣ መርዝን በመርዝ፣ ጦርነትን በጦርነት፣ ዘረኝነትን በዘረኝነት፣ ነጭን በጥቁር፣ እንግሊዘኛን ባማረኛ።
አንድ ሐረግ ሲመዘዝ ደን ይወዘወዛልና፣ ወሬ ቢበዛ ባህያ አይጫንምና፣ ምክር ሲበዛ ዝክር ይሆናልና፣ ማርም ሲበዛ ይመራልና፣ አንዳንድ እጽዋቶች ደግሞ የሚለመልሙት ሲቆረጡ ነውና፣ ሐተታየን እዚህ ላይ ልቁረጥ፡፡ በቃኝ፡፡
መስፍን አረጋ
mesfinamharic.com
mesfinarega.com
mesfin.arega@gmail.com